እግዚአብሔር ዳዊትን “እንዴ ልቤ” ያለበት ምክንያት ምንድን ነው? ክፍል አምስት

 


5. የቅባትን ሚስጢር አውቆ ማክበሩ

*      ዳዊት የተቀባ ሰው ቢሆንም ሳኦል ከእርሱ በፊት ተቀብቶ የነገሠ የእግዚአብሔር ቅባት ያለበት ሰው መሆኑን ያውቃል፡፡ ስለዚህም ዳዊት የተቀቡ የእግዚአብሔር ሰዎች ላይ ክፉ ነገር ማድረግ(ቅባትን መዳሰስ) በእስራኤል ህግ የሚያመጣውን ርግማን ያነበበ/የተማረ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ መዝ.105፡14-15 (1ኛ ዜና.16፡21-22) “የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።”(He suffered no man to do them wrong: yea, he reproved kings for their sakes, Saying, Touch not mine anointed, and do my prophets no harm.).

*      ብዙ ሰዎች “ቅባትን መዳሰስ (Touching anointed) ምን ማለት እንደሆነ እንደ ቃሉ የተረዱት አይመስለኝም፡፡ ለካህን በተገቢው መንገድ አሳብ መስጠት፣ ትክክል ያልሆነበትን እንዲስተካከል በፍቅር መናገር…ወዘተ ቅባትን መዳሰስ ይመስላቸውና ካህናትን ከስህተት ከመጠበቅ ይልቅ ሲጠፋ ዝም ብሎ ማየትን ይመርጣሉ፡፡ ካህናት ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ሰዎች ብሆኑም ሰዎች ስለሆኑ ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም አንድ ካህን ቢሳሳት ስርዓት ባለው መልኩ መሳሳቱን ነግሮ ከስህተቱ እንዲታረም ማድረግ ቅባት መዳሰስ ሳይሆን ለካህኑ ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡

*      ለምሳሌ የሳዖል የሠራዊቱ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር ሳኦል ዳዊትን ከማሳድ እንዲመለስና ወደ ሌላ ተግባራት እንዲያተኩር አንድም ቀን ምክር ሲለግስ አልታየም፡፡

*      1ኛ ሳሙ.26፡15-16 “ዳዊትም አበኔርን። አንተ ጕልማሳ አይደለህምን? በእስራኤል ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? ጌታህን ንጉሡን ለመግደል አንድ ሰው ገብቶ ነበርና ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቅ ስለ ምን ነው? ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም ሕያው እግዚአብሔርን! እናንተ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና ሞት ይገባችኋል አሁንም የንጉሡ ጦርና በራሱ አጠገብ የነበረው የውኃው መንቀል የት እንደ ሆነ ተመልከት አለው።” አበኔርም መጨረሻው አላማረም ኢዮአብ ሆዱን ወግቶ ገድሎታል (2ኛ ሳሙ.3፡27 እና 30)፡፡

*      “ቅባትን መዳሰስ (Touching anointed) ማለት እግዚአብሔር በቀባው ሰው ላይ(የተቀባው ሰው ጥፋት ቢኖርበትም ባይኖርበትም) ለዚያ ካህን አለመታዘዝ፣ ተንኮል ማሰብ፣ ክፉ ነገርን ማድረግ፣ ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መፈጸም፣ መምታት  ወይም መደብደብ፣ ማደም፣ ማቃለል፣ መሳለቅ፣ ማፌዝ፣ መናቅ፣ ማስጨነቅ፣ በማስፈራራት ከስፍራው እንዲነሳ መድረግ…ወዘተ ማለት ነው፡፡

*      1ኛ ሳሙ.24፡1-6 “…የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገረህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቈረጠ።ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቈረጠ የዳዊት ልብ በኀዘን ተመታ  እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው”፤

*      1ኛ ሳሙ.26፡1-21 “…አቢሳም ዳዊትን፦ ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፥ ሁለተኛም አያዳግምም አለው። ዳዊትም አቢሳን፦ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው አለው። ደግሞም ዳዊት፦ ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል… ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ አለ።”

*      በ2ኛ ሳሙ.1፡1-16 “…ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው። ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ። ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም። ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው።”

*      2ኛ ሳሙ.19፡18-23 “…የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን፦ ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት የተገባው አይደለምን? አለ።…”(2ኛ ሳሙ.16፡5-8 እና ቁ 13 የሳሚ ስድብ)፡፡

*      የእግዚአብሔርን መልዕክተኞች መናቅ በእስራኤላውያን ላይ ትልቅ ቅጣት አስከትሎባቸው ነበር፤ 2ኛ ዜና 36፡15-21 “የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር።እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።”

*      እኛ በእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በነቢያቱም ጭምር እንድናምን ታዘናል፤ 2ኛ ዜና 20፡20 “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ። (Believe in the Lord your God, so shall ye be established; believe his prophets, so shall ye prosper.)

*      የዳዊትን የቅባት አረዳድን ለየት የሚያደርገው  ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ አበኔር የተመረጡ 3000 ሰራዊት አሰልፈው ዳዊትን ለመግደል ሲመጡ እግዚአብሔር በሳኦልና በሠራዊቱ ላይ የእንቅልፍ መንፈስ ለቅቆባቸው በዳዊት እጅ አሳልፎ ቢሰጣቸውም ዳዊት ገድሎ ዙፋኑን መረከብ ሲችል የኋላ ኋላ ቅባት የሚያስከፍለውን ዋጋ ስለተረዳ አላደረገውም፡፡ ይልቅስ  “ዳዊት፦ ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል (1ኛ ሳሙ.26፡1-21)” ይል ነበር፡፡ እንዳለውም ሆነ፡፡

*      ሳኦል ግን ዳዊትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ በትክክል ቢያረጋግጥም የእርሱን ቅባት ማክበር አቅቶት ለውድቀት ተዳረገ፡፡ እግዚአብሔር የቀባቸው ካህናት ቅባት ወደ ላይም ወደ ታችም መከበር አለበት፡፡

Post a Comment

Previous Post Next Post