4. እግዚአብሔር ስፍራና ማደሪያ ያገኝ ዘንድ መጨነቁ
ዳዊት በሳኦል ተሰድዶ ለበርካታ ዓመታት በስደት ጫካ ውስጥ ሲኖር እረፍት
የነሳው ጉዳይ ከመች መች ሳኦል ሞቶ ከጫካ ወጥቼ እፎይ ብዬ እኖራለሁ ሳይሆን ጫካ ውስጥ ለዓመታት ተረስቶ የቆየው የእግዚአብሔር
ታቦት ከጫካ ወጥቶ በመቅደስ ውስጥ ስያርፍ ማየት ነው፡፡
ሐዋ.7፡44-50 “አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው
ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች።እርሱም በእግዚአብሔር ፊት
ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ። ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት። ነገር ግን ነቢዩ። ሰማይ
ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው?
ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም።”
2ኛ ዜና 6፡2-7 እና 1ኛ ነገ.8፡13-17 “…አባቴም ዳዊት ለእስራኤል
አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ።”
መዝ.(132)፡1-6
|
1 አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ |
|
2 ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ። |
|
3 በእውነት ወደ ቤቴ
ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ
አልወጣም፥ |
|
4 ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ |
|
5 ለእግዚአብሔር ስፍራ፥
ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። |
|
6 እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር
ውስጥም አገኘነው። |
በኤሊ ዘመን በጠላት የተማረከውን የእግዚአብሔርን ታቦት መፈለግና ከጫካ
አውጥቶ መቅደስ ሰርቶ የማስቀመጥ ተግባር የንጉሡ የሳኦል ነበር፡፡ ሳኦል ግን ተግባሩን ትቶ ዳዊትን ማሳደድና መግደልን የእለት
ተእለት ተግባር አድርጓል፡፡ 1ኛ ዜና 13፡3 ላይ “በሳኦልም
ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ
አላቸው።” ይላል፡፡ ዳዊት ሳኦልን ብቻ ሳይሆን እስራኤልን በሙሉ ለታቦቱ አለመፈለግ ተጠያቂ ሲያደርግ እናያለን፡፡
ዳዊት ለራሱ
ከጫካ ለመውጣትና እረፍት ስጠኝ ብሎ ስዕለት መሳል ሲችል ታቦቱ ከጫካ መውጣት የሚሳል፣ ለራሱ ስፍራ ያላገኘ ለታቦቱ ስፍራ የሚፈልግ፣
ለራሱ ማደሪያ ያላገኜ ለታቦቱ ማደሪያ የሚፈልግ የሚገርም የእግዚአብሔር ልብ ያለው ወጣት ነው፡፡
ሳኦል እግዚአብሔር ዙፋን ላይ አስቀምጦት ታቦቱን ለማምጣት ሳይሆን ዳዊትን
ለማጥፋት ይፈልጋል፤ ዳዊት ግን እየተሰደደ ታቦቱን ይፈልጋል፡፡
ዳዊት ለታቦቱ ማደሪያ ሊያገኝ ስለወደደ እግዚአብሔርም ዳዊትን ለዘላለም
ወደደው፡፡ 1ኛ ዜና 28፡4 “ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የዘላለም ንጉሥ እሆን ዘንድ ከአባቴ ቤት
ሁሉ መርጦኛል ይሁዳም አለቃ ይሆን ዘንድ መርጦታል ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሠኝ ዘንድ ሊመርጠኝ ወደደ፡፡” 2ኛ ዜና 6፡6 “ነገር ግን
ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል
ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ ብሎአልና።”
ዛሬም ታቦቱ ማረፍያ መቅደስ(ያልዳኑትን ነፍሳት) እየፈለገ ጫካ ውስጥ(በዓለም
ዙሪያ) ይንከራተታል፡፡ ማን ነው ታዲያ ለእነዚህ ነፍሳት ወንጌል መስክሮ ታቦቱን የሚያሳርፍ፡፡ አሁን የእግዚአብሔር ማረፊያ በወንጌል
የዳኑ ነፍሳት ናቸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት(በ2020 እ.አ.አ) የዓለም ህዝብ ቁጥር 7.9 ቢሊዮን ነው፤
በኢየሱስ ስም ተጠምቀውና በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የእግዚአብሔር መደሪያ የሆኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ የቤተክርስቲያናችን ምዕመናን
6 ሚሊዮን አይሆኑም፡፡ 7.894 ቢሊዮን ህዝብ ወንጌል አላገኘም፡፡
- በዓለም አቀፍ ደረጃ 7,900,000,000-6,000,000 =
7,894,000,000 ሰዎች አልዳኑም (ታቦቱ ማረፍያ አላገኘም)
- በኢትዮጵያ ደረጃ 120,000,000-5,000,000 =
115,000,000 ሰዎች አልዳኑም (ታቦቱ ማረፍያ አላገኘም)
-በአርባምንጭ ከተማ ደረጃ 192,000-5,000 = 187,000 ሰዎች
አልዳኑም (ታቦቱ ማረፍያ አላገኘም)
ዳዊት ታቦቱን
ለማስመለስ ሁኔታዎች በማይፈቅዱ ሰዓት ነበር ምኞቱ ማቃጠል የጀመረው፤ እንዲያውም “በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ቀረ” (1ኛ ሳሙ.20፡3) እያለ ግን የታቦቱ ነገር ያቃጥለዋል፡፡ ይህ
የሚያሳየን የሚጠፉ ነፍሳት ቅናት ሊያቃጥለን የሚገባው ቦታ ባልተሰጠንና በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጭምር ሊጀምረን ይገባል ማለት
ነው፡፡ ነፍሳትን የማዳን ጉዳይ ከቦታ/ከስልጣን ጋር ምንም አያገናኘውም ማለት ነው፡፡
2ኛው መንፈሳዊ ትርጉም እኛ የዳንን ሰዎች እግዚአብሔር በውስጣችን አርፎ
እንዲቀመጥ ተመችተነዋል ወይ? ወይስ ከቃሉ ውጪ እየተጓዝን ኢየሱሰን እየበደልን ከውስጣችን አባረነዋል?
እግዚአብሔር ታቦቱ እንዲያርፍለት የሚፈልገው በጽዮን ተራራ ላይ ነው፡፡
መዝ 132፡13-14 “እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ
ብሎ። ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።”
1ኛ ቆሮ.3፡16-17 “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም
መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር
ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”
2ኛ ቆሮ.6፡16 “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም
አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም
እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”
መዝ.24፡9-10 “እናንተ መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም
ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ።ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።”
መዝሙረ ዳዊት 84፡1-7
“የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው!...
7 ከኃይል
ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።”
መዝ. 102፡16 “እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና።” ሲል በአዲስ ኪዳን ጌታ ኢየሱስ በልጆቹ
ላይ ተገልጦ እንደሚታይ የሚጠቁም ትንቢታዊ ቃል ነው፡፡ ኢሳ.
60፡-1-3 “ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ።እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም
አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል
ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።”
እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ በታቦቱ ውስጥ የሚቀመጠውን ጽላት ላይ የተጻፈውን
10ቱን ትዕዛዛት ሲሰጥ 3000 ሰዎች መተዋል (ዘጸ.32፡28)፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በጽዮን በበዓለ 50 ቀን መንፈስ ቅዱስን
በሰጠ ቀን 3000 ሰዎች ድነዋል፡፡
