3. ስፍራ ወይም ስልጣን ፈላጊ አለመሆኑ
ሌላው እግዚአብሔር ከዳዊት ህይወት ደስ የተሰኘበት ዳዊት ከተቀባም በኋላ
የበግ እረኝነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል እንጂ “አሁን ተቀብቻለሁና በጎቻችሁን ተረከቡ ሌላ የሚመጥነኝን ስፍራ ስጡኝ” አላለም፡፡
የእግዚአብሔር መንግስት ስልጣን እኛ ስለፈለግን የምናገኘው ሳይሆን እግዚአብሔር
ራሱ ስለፈለገን የሚሰጥ መለኮታዊ የአመራር ጸጋ ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12፡28
“እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት
ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥
የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።”
1ኛ ሳሙ.16፡19 “ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ። ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ።… እንዲህም ሆነ
ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና
ይዞ በእጁ ይመታ ነበር ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥
ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።”
በመጽሐፍ ቅዱስ ውሰጥም ሆነ በዚህ ዘመን ሙዚቃ መሳሪያ በመጫወት ብቻ ክፉ
መንፈስን ያባረረ ሰው ከዳዊት ውጪ የለም፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ ነገር ግን ይህም ቢሆን ዳዊትን ስፍራ ፈላጊ አላደረገውም፤
አሁንም እርሱ ከበጎቹ ጋር ነው፡፡ 1ኛ ሳሙ.17፡15 “ዳዊትም
የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር።”
እግዚአብሔር ራሱ የዳዊት መታያ ጊዜ ሲደርስ ፍልስጤማውያን ነገር እንዲፈልጉ
አደረገ፤ 40 ቀን ሙሉ ጎልያድ ሲፎክርና እስራኤላውያንን እጅግ ሲያስደነግጣቸውና ሲሸሹ ቆዩ፡፡ አንደ አጋጣሚ ለወንድሞቹ ስንቅ
እንድያደርስ በአባቱ የተላከው ዳዊት ስንቅ ይዞ በወጣው እጁ የእስራኤልን ጠላት የጎልያድን ራስ ይዞ ተመለሰ፡፡
አያችሁ ባላችሁበትና በስፍራችሁ በትዕግስትና በጥሩ ልብ እያገለገላችሁ ኑሩ
እንጂ የእናንተ ጊዜ ሲደርስ ድንገት በወጣችሁበት ድል አድርጋችሁ ምርኮ ይዛችሁ ትመለሳላችሁ፡፡
ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ እየመጣ እያለ ሳኦል በጦር አለቃው በአቤኔር
ዳዊትን አስጠርቶ የእሴይ ልጅ መሆኑን ከተረዳ በኋላ “በል ከአሁን በኋላ ወደ አባትህ ቤት አትመለስም” ብሎ ከራሱ ጋር ማኖር ጀመረ፡፡
1ኛ ሳሙ.18፡2 “በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም
ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም።”
ይህ የዳዊት ስልጣን ፈላጊ አለመሆን በእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ዳዊት በዮናታንም
ልብ ትልቅ ስፍራ እንዲይዝና እንደ ነፍሱ እንዲወደው አድርጎታል፡፡ ዮናታን የሚገርም ልጅ ነው፡፡
1ኛ ሳሙ.18፡3 “ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል
ኪዳን አደረገ። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን
ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው” ይላል፡፡
የንጉስ ልጅ ሆኖ፣ ቀጣይ አልጋ ወራሽ ሆኖ ከእርሱ የተሻለ ሰው ሲገኝ “እኔ አይገባኝም” ብሎ ሙሉን ክብሩን አውልቆ መስጠት ተደርጎ የማይታወቅ ከዳዊት ድል የማይተናነስ ተግባር ነው፡፡
እኛ ብንሆን ምላሻችን ምን ይሆን ነበር?
ይህ የዮናታን ተጋባር የሚያሳየው ምንም እንኳ አሁን ዳዊት በአባቱ ዘንድ
ቦታ ተነፍጎት ተሳደጅ ቢሆንም አንድ ቀን እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ እንደሚያደርገው የተረዳ ይመስላል፡፡
ዮናታን በ1ኛ ሳሙ.23፡17-18 “የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥
እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ (አንተ አንደኛ ሁን ማለቱ
ነው) ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል አለው።ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ ዳዊትም በጥሻው ውስጥ
ተቀመጠ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ሄደ።”
ከዚህ በኋላ ከሳኦል ለዳዊት የተሰጠው ተግባር ሳኦል ወደ ሚሰደው ሁሉ መሄድና
በገና መደርደር ነበር፤ ዳዊት ግን አሁንም ተግባሩን አስተውሎ ያደርግ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ከዳዊት ጋር ነበር፡፡
በመንፈሳዊው ዓለም ማስተዋል ያለብን ሰዎች በአንድ ቸርች ውስጥ እያገለገሉ
ሳሉ ለስልጣንና ለራሱ ክብር ከሚጨነቀው ሰው እግዚአብሔር ይለያል ለእግዚአብሔር ክብር ከሚጨነቀው ጋር እርሱ ይሆናል፡፡
የዳዊት የመጀመሪያ ሹመት ሻለቃነት ነበር፡፡ ይህን ስልጣን ዳዊት አመልክቶ
ሳይሆን እንዲያውም ሳኦል ዳዊት ላይ ተንኮል ስላሰበና ከአጠገቡ አርቆ ለመግደልና ለማስገደል ስለፈለገ ነበር፡፡ ነገር ግን የሳኦል
አሳብ ሊሳካ አልቻለም፤ እንዲያውም እግዚአብሔር ለዳዊት በህዝቡ ፊት ሞገስ ሰጠው፡፡
1ኛ ሳሙኤል
18፡12-17 “ግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥
የሺህ አለቃም አደረገው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።
ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው።ነገር
ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።ሳኦልም ዳዊትን፦ ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን
እድርልሃለሁ፤ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት
ተጋደል አለው። ሳኦልም፦ የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን ይል ነበር።”
ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ተጠቅሞ ዳዊትን በቤቱ ሊያስገድለው እንደሆነ የሰማችው
ሚስቱ ሌሊት በመስኮት አስመልጣው ዳዊት የጫካ ኑሮውን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡
1ኛ ሳሙኤል
19፡11-17 “ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስቱም ሜልኮል፦ በዚህች ሌሊት
ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው።ሜልኮልም ዳዊትን
በመስኮት አወረደችው፤ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ።ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል
ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው።ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም፦ ታምሞአል አለቻቸው።ሳኦልም፦ እገድለው
ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ።መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ
አገኙ፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ።ሳኦልም ሜልኮልን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኰበለልሽው
አላት። ሜልኮልም ለሳኦል፦ እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት።”
ዳዊት የእስራኤል ነፃ አውጪ ግንባር አቋቁሞ ሳኦልን ገድሎ ንግስናውን መረከብ
አልፈለገም፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር ዳዊት ሊገድሉ ጫካ በመጡ በሳኦልና ሰራዊቱ ላይ የእንቅልፍ መንፈስ ለቆባቸው በዳዊት እጅ
ጥሏቸው ነበር፤ ነገር ግን ዳዊት የስልጣን ጥማት ቢኖረው ኖሮ ሳኦልን ገድሎ ወይም በጋሻ ጃግረዎቹ አስገድሎ ንግስናውን መረከብ
ይችል ነበር፤ ግን የስልጣን ጥማት ስላልነበረው አላደረገውም፡፡
