እግዚአብሔር ዳዊትን “እንዴ ልቤ” ያለበት ምክንያት ምንድን ነው? ክፍል ሁለት

 


2. የከበረውን ከተዋረደው መለየት መቻሉ

*      ኤር.15፡19 “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም።”

*      ዳዊት የከበረውን ከተዋረደው መለየት የሚችል ትልቅ ማስተዋል እግዚአብሔር የሰጠው ልጅ ነው፡፡

*      1ኛ ሳሙ.17፡28-29 “ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ የኤልያብም ቍጣ በዳዊት ላይ ነድዶ። ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው። ዳዊትም፦ እኔ ምን አደርግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን ? አለ”፡፡ ዳዊት ከጠላት መዋጋት ከበግ ጋር ከመዋል የሚበልጥና የከበረ ታላቅ ተግባር መሆኑን የተረዳ ልጅ ነው፡፡

*      በጦር መዳ ላይ መዋጋት ማለት ትርጉሙ ዛሬ ምስክርነት፣ ጾምና ጸሎት ማለት ነው፡፡ መስካሪነት ታላቅ ተግባር ነው፡፡ መስካሪነት ጦረኝነት/ ወታደርነት ነው፡፡

*      በአዲስ ኪዳን ከተነሱት የእግዚአብሔር ሰዎች ስለ ጦርነትና ወታደርነት ምንነት በስፋት የተናገረውና የተገበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፡፡ ጳወሎስ የከበረውን ከተዋረደው መለየት የቻለው ወዲያውኑ እንደተጠራ ነበር፡፡

*      ፊል 3፡4-11 “እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው  ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።ዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።”

*      ሐዋርያው ጳውሎስን ከዳዊት ጋር ከሚያመሳስሉት ነገሮች ዋነኛው የእግዚአብሄርን ጦርነት ወይም ከጠላት ጋር የሚደረገውን ተጋድሎ ዋነኛና ታላቅ ተጋባር ማድረጉ ነው፡፡

*      ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጦርነትና ውጊያ ለጢሞቴዎስ ከተናገራቸው የተወሰኑትን እንመልከት፡-

*      1ኛ ጢሞ.6፡12 “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ”፡፡

*      1ኛ ጢሞ.1፡18 “ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤”

*      2ኛ ጢሞ.2፡3 “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም።ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም፡፡”

*      ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ሐዋርያቱን 3 ዓመት ተኩል ካስተማራቸው በኋላ የተናገራቸው ዋናና ትልቁ ተግባራቸው ምስክርነት መሆኑን ነው፡፡ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።” (ሐዋ.1፡8)፡፡

*      ሐዋርያው የአስቆሮቱ ይሁዳ ለዚህ ለከበረ ተግባር ተጠርቶ እሱ ግን የከበረውን ከተዋረደው መለየት ስላቃተው በገንዘብ ፍቅር አብዶ ፈንድቶ/ሆዱ ተዘርግፎ ሞተ “ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበርና፥ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና” (ሐዋ.1፡17)፡፡

*      ሳኦል ለዚህ ለከበረ ተግባር ተጠርቶ እሱ ግን የከበረውን ከተዋረደው መለየት አቃተው፡፡ 1ኛ ሳሙ.9፡20 “ከሦስት ቀንም በፊት የጠፉ አህዮችህ ተገኝተዋልና ልብህን አትጣልባቸው። የእስራኤል ምኞት ለማን ነው? ለአንተና ለአባትህ ቤት አይደለምን? አለው”፡፡ እንደገና 1ኛ ሳሙ.10፡1  ላይም “ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው፦ በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ።” ተብሎ ነበር፡፡

*      ሳኦል ግን ከተቀባም በኋላ ልቡን ከአህዮች ላይ ማንሳት አቅቶት የመንግስትን ነገር መናገር ሲያዳግተው እናያለን፡፡  1ኛ ሳሙ.10፡16 “ሳኦልም አጎቱን፦ አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን አለው ነገር ግን ሳሙኤል የነገረውን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም።”

*      ሙሴም በወጣትነቱ የከበረውን ከተዋረደው መለየት የቻለ ልጅ ነበር፤ በዚህም ምክንያት በእርሱ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ፕሮግራም እስከ ጫፍ አድርሶና ለተተኪ አስረክቦ ወደ ወገኖቹ ሲከማች እናያለን፡፡

*      ዕብ.11፡24-27 “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።”

Post a Comment

Previous Post Next Post