የትምህርቱ መነሻ ጥቅሶች
1ኛ ሳሙ.13፡14 “አሁንም መንግሥትህ አይጸናም እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው።” ፡፡
ሐዋ.13፡22 “እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም። እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።”
ሐዋ.13፡36 “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤” ዕብ.10፡36 “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።”
1ኛ ዮሐ.2፡17 “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”
መግቢያ
ክርስትና መጀመርና መጨረስ ያለው ታላቅ ሩጫ ነው፤ መጨረስ የሌለው ክርስትና ከንቱ ድካም ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ(በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን) ይንን ታላቅ ሩጫ ጀምረው የጨረሱና ያልጨረሱ ሰዎች አሉ፤ ዳዊት ግን በጥሩ
ሁኔታ ሩጫቸውን ከጨረሱት መካከል ቀዳሚ መሆኑን እግዚአብሔር “እንደ ልቤ የሆነ ሰው” በማለት መስክሮለታል፡፡
የዳዊትን ህይወት ማጥናት የክርሰስትናን ሙሉ ፓኬጅ (ከጅምር እስከ ፍፃሜ) ማጥናት ስለሆነ እጅግ ይጠቅመናል፡፡ የዳዊት
ህይወት በተለይ እንድናጠና ከሚያደርገን ጉዳይ ዋነኛው እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ካሉ ብዙ ታላላቅ የእግዚአብሔር
ሰዎች ዳዊትን ብቻ “እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ” ማለቱ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ህይወታቸውን ሙሉ ለእግዚአብሔር ሥራ ያዋሉና ብዙ ታላላቅ ሥራ የሰሩ ሰዎች፣ ከዳዊት የተሻሉ
ናቸው የምንላቸው፣ በጽድቅና በቅድስና ከዳዊት የሚበልጡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እንደ ዳዊት እንደ ልቤ አልተባሉም፡፡ ዳዊት
ከእግዚአብሔር ሰው የማይጠበቅ ታላቅ የሚባል ኃጢአት የሰራ ሰው ሆኖ ሳለ “እንደ ልቤ” መባሉ በዳዊት ህይወት
እግዚአብሔር ያየው ለየት ያለ ነገር መኖሩን የሚያመለክት ነው፡፡ የዳዊትን ሕይወት ለማጥናት በዳዊት ዘመን የነበሩትን
የሌሎች የእግዚአብሔር ሰዎችን ህይወት አብሮ ማጥናት የዳዊት የአካሄድ ልዩነቱን በደንብ ለመረዳት ይረዳናል፡፡
የሳሙኤልን መጽሐፍ ስናጠና የመሳፍንት ዘመን ማብቅያ ላይ የነበረውን ካህኑን ኤሊን ያስተዋውቀናል፡፡ በኤሊ ዘመን
የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ እንደነበርና ራእይም እንደማይገለጥ ይናገራል (1ኛ ሳሙ.3፡1)፡፡ በዚህ ዘመን ብላቴናው
ሳሙኤልን እግዚአብሔር ለሐና ሰጥቶ እሷም ለእግዚአብሔር ሰጥታው በእስራኤል ላይ ፈራጅ እንዲሆን በብላቴናነቱ
ድምጹን ያሰማውና መጠቀም የጀመረው ሰው ነው፡፡ ሳሙኤል የእስራኤል የመጨረሻው መስፍን ነው፡፡ ኤሊ ሲሸመግል
ልጆቹ በመንገዱ ባለመሄዳቸው ምክንያት ህዝቡ ንጉሥ እንዲያነግስላቸው ሳሙኤልን ጠየቁት፡፡ በዚህ ወቅት ነው
የመጀመሪያ የእስራኤል ንጉሥ የቂስ ልጅ ሳኦል የተቀባው ( 1ኛ ሳሙ. 10፡1)፡፡ ሳኦል ከሁለት የንግስና ዓመት በኋላ አካሄዱን
በማበላሸቱ ወዲያውኑ ዳዊትን እንዲቀባው ሳሙኤልን ወደ እሴይ ቤት እግዚአብሔር ልኮት ዳዊት ተቀባ፤(1ኛ ሳሙ.16፡13)፡፡
የሳኦልንና የዳዊትን የአቀባብ ሁኔታ ስንመለከት ሳኦል የጠፉ የአባቱን አህዮች ፍለጋ በወጣበት የተቀባ ሲሆን ዳዊት ደግሞ
የአባቱን በጎች ሲጠብቅ የተቀባ ሰው ነዉ፡፡ ዳዊትና ሳኦል ሁለቱም በሳሙኤል የተቀቡ ናቸው፤ ሁለቱም ሳያስቡ የተቀቡ
ናቸው፡፡ ከቅባት በኋላ ሳኦል ትንሽ ተጉዞ አካሄዱ ሲበላሽና ከእግዚአብሔር ፊት ሲወድቅ ወይም ሲጣል እንመለከታለን፤
ዳዊት ግን እስከ ፍፃሜ ድረስ በጥሩ ልብና መንፈስ ሄዶ እንደ ልቤ ተብሎ ጨርሷል፡፡
ስለዚህ ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ፕሮግራምና ጥሪ በሕይወታችን ቢኖርም በእኛ ላይ ያለው የእግዚአብሔር አሳብ
እንዲፈጸም የራሳችን ድርሻ ከፍተኛ ስፍራ እንዳለው ከዳዊትና ከሳኦል ህይወት እንማራለን፡፡ እንደፈለጉ እየኖሩ
እግዚአብሔር በእኔ ህይወት ያየው ነገር ይሆናል ማለቱ አለማስተዋል ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀውን ካልተወጣን እግዚአብሔር
መንገድ ላይ ይተወናል፡፡ ለውድቀታችንም ሆነ ለስኬታችን የእኛ ድርሻ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ስኬታማ
ሰው ማለት ብዙ ህዝብ ማግኘት፣ ብዙ ወዳጅ ማፍራት፣ ብዙ ክብር ማግኘት፣ ወዘተ… ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ሊሰራ
ያሰበውን መለኮታዊ ፕሮግራም እስከመጨረሻው ሳያበላሹ ከዳር ማድረስና መጨረስ መቻል ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠርቶ
ከቀባን በኋላ የሚጸጸትብን ሰዎች (እንደ ሳኦል) እንዳንሆን ማስተዋል አለብን፡፡ 1ኛ ሳሙ.15፡35 “እግዚአብሔርም
በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ” ይላል፡፡
በጣም የሚያስደነግጠው እግዚአብሔር ሰዎች በቤቱ እያሉ ቆርጦ ሊጥላቸው መቻሉ ነው፤ በሥጋቸውም ምንም ላይሆኑ
ይችላሉ፤ ከመንፋሳዊው ዓለም የተቆረጠ ሰው በሥጋዊው ዓለም ምንም ሳይሆን በመንፈሱ ሙት ሆኖ ይኖራል፡፡
እግዚአብሔር በሥጋቸው ቀጥቶና አስተምሮ የሚመልሳቸው ሰዎች ቀና እና ምልስ ልብ ያላቸው መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ
ነው፡፡ እንደ ሳኦል እልከኛ ልብ ያለውን ሰው እግዚአብሔር የሚቀጣው ዝም በማለትና በመተው ነው “ሳኦልም
እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።” (1ሳሙ.28፡6)፡፡
እግዚአብሔር ትልቁ ቅጣት ዝምታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዝም ያለው ሰው መፍራትና መደንገጥ አለበት፡፡ ሳኦል በጥሩ ልብና
መንፈስ እግዚአብሔርን ያገለገለው ለሁለት ዓመት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ከ37 ዓመት በላይ ያለ እግዚአብሔር ንጉሥ ሆኖ
ኖሯል፡፡ በጣም የሚገርመው እግዚአብሔር ሳኦልን ከመንፈሳዊው ዓለም ቢቆርጠውም ጤናውን፣ ንግስናውን፣ ሰራዊቱን፣
ገንዘቡን፣ ክብሩን… ወዘተ አልወሰደበትም፡፡ ስለዚህ በቤቱ ለሥጋችን ተመችቶን መኖራችን ብቻውን እግዚአብሔር ጋር
ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የመኖራችን ምልክቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ሳይበላሽና
ሳይቋረጥ በጥሩ ልብና መንፈስ መኖራችን ብቻ ነው፡፡
እኛ ትልቅ የእግዚአብሔር ፕሮግራም ያለብን ሰዎች ነን፡፡ እርሱ እኛን የዚህ ዘመን ዳዊቶች እንዲንሆንለት ይፈልጋል፤
ይጠብቃልም፡፡ ዛሬ በግ ጥበቃ ላይ ወይም አህያ ፍለጋ ላይ ልንሆን እንችላለን፤ ነገር ግን ትልቅ የእግዚአብሔር ፕሮግራም
እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡ የዳዊት ያን የመሰለ ትልቅ የእግዚአብሔር ፕሮግራም በላዩ ላይ እያለ ወላጆች ዳዊትን
በሳሙኤል ለመቀባት ከወንድሞቹ ጋር ለምርጫ እንኳን አላቀረቡትም ነበር (1ኛ ሳሙ.16፡6-13)፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር
ጣልቃ ገብቶ እንዲቀባ አድርጎታል፡፡ ሰይጣን በአንተ ላይ የእግዚአብሔር ፕሮግራም እንዳለብህ ሲያውቅ ለማደናቀፍ
ሰዎችን ያስነሳብሃል፡፡
ሰይጣን ዳዊት ለትልቅ የእግዚአብሔር ፕሮግራም መፈለጉን ሲያውቅ በመጀመሪያ የራሱን ወላጆች አስነስቶ ለምርጫ
እንዳያቀርቡት አስደረገ፤ ቀጥሎ ወንድሙ ኤልያብን አስነስቶ አስሰደበው (1ኛ ሳሙ.17፡28-30) “…እኔ ኵራትህንና የልብህን
ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው።…ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥”፡፡ ከዚያም ዘማሪዎችን
ተጠቅሞ አስዘመራቸው (1ኛሳሙ.18፡6-9) “እንዲህም ሆነ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና
እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። ሴቶችም።
ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ
ተመለከተው”፡፡
ኤልያብ ግፋ ቢል ሻለቃ የመሆን ፕሮግራም ነው ያለበት፤ ዳዊት ግን ንጉሥ የመሆን ፕሮግራም አለበት፡፡ ለዚህ ነው
ከወንድሙ ጋር ተጋጭቶ ከማበላሸት ዘወር ያለው፡፡ ዳዊት ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ፕሮግራም ለማጨናገፍ ሰይጣን
የውጪ ጠላት ፍላፃ ሳይሆን የውስጥ ፍላፃ ነው ያስወረወረበት፤ (ከቤተሰቡ፣ ከመዘምራን እና ከንጉሡ ሳኦል)፡፡ የውጪውን
ጠላት (ፍልስጤማውያንን) ዘርሮ እንደሚያሸንፍ ሰይጣን ያውቅ ነበርና፡፡ ስለዚህ በእኛ ላይ ያለው የእግዚአብሔር
ፕሮግራም ከጫፍ እንዲደርስ ሰይጣን ከውጪና በተለይ ከውስጥ የሚያስነሳብንን ፍላፃዎችን በማስተዋልና በጥበብ ለማለፍ
እግዚአብሔር ጥሩ ልብ እንዲሰጠን መጸለይ አለብን፡፡ ከዚህ ቀጥለን ዳዊት እንደ ልቤ የተባለበት ምክንያቶች ይሆናሉ
ያልኳቸውን ነጥቦች ቀጥሎ አቀርባለሁ፡፡
